Web Content Display Web Content Display

 "የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ያለፈውን ፣ያሁኑንና መጪውን ትውልድ የሚያስተሳስር ተቋም"

          መግቢያ   

መረጃ ለሀገር ልማት፣ ለትምህርት ዕውቀት መስፋፋት፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ መዳበር በተለይም አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለዘመን አቻ የማይገኝለት መሣሪያ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ መረጃ ባግባቡ ተሰብስቦና ተደራጅቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ከተደረገ የህብረተሰቡን ችግር በመቅረፍ በኩል የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ደግሞ አብያተመዛግብት፣ አብያተመጻሕፍትና የዶክመንቴሽን ማዕከላት ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይዘው ይገኛሉ፡፡

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ የሀገሪቱ ብሔራዊ የመረጃ ማዕከል እንደመሆኑ የሀገሪቱን የሥነ-ፅሁፍ ሀብቶችና ቅርሶች በአንድ ማዕከል ስር በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና ጥቅም ላይ በማዋልና ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡

የኤጀንሲው ታሪካዊ ዳራ

የዛሬው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ

· “የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር” በሚል ስያሜ በ1936 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን፤አገልግሎት መስጠት የጀመረውም ንጉሱ ባበረከቱት የመጻሕፍት ስጦታ ነው፣

· በ1958 ዓ.ም በተደረገው የቤተመጻሕፍት መዋቅር ለውጥ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት የሚል ስያሜ ይዞ በጥንታዊ ቅርሶች አስተዳደር ስር እንዲሠራ ተደረገ፣

· በ1967 ዓ.ም በመምሪያ ደረጃ ተዋቅሮ ስራውን ቀጠለ፣

· በ1968 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 5ዐ/68 ለባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚ/ር በሀገር ውስጥ ከሚታተሙ ማናቸውም ህትመቶች ሶስት ሶስት ቅጂዎችን እንዲረከብ በመንግስት የተሰጠውን ስልጣን ቤተመጻሕፍቱ እንዲያስፈፅም ውክልና አገኘ፣

· በ1972 ዓ.ም ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት መምሪያ ተብሎ ስራውን እንዲያከናውን ተደረገ፣

· በ1986 ዓ.ም በተደረገ የመዋቅር ለውጥ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ድርጅት የሚል ስያሜ ይዞ እንዲሰራ ተደረገ፣

· የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ድርጅት በአዋጅ ቁጥር 179/91 በሀገሪቱ የሚገኙ መዛግብትን፣ መጻሕፍትንና መሠል ጽሁፎችን በአንድ ማዕከል ስር በማሰባሰብና በማደራጀት የሀገሪቱን የመረጃ አገልግሎት በተቀናጀ ሁኔታ መምራት የሚያስችለውን ህጋዊ ሰውነት አገኘ፡፡

             · በ1998 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው አዋጅ ቁጥር 471/98 የአስፈጻሚ መ/ቤቶች ስያሜ                           መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና  ቤተመጻሕፍት ድርጅት - ኤጀንሲ በሚል መጠሪያ እንዲለወጥ                   ተደርጎ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡